Zehabesha: የትግራይ ተወላጆች “በጦርነት ሳቢያ ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጠየቁ

የትግራይ ተወላጆች “በጦርነት ሳቢያ ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጠየቁ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

 0  465  465

(አቻምየለህ ታምሩ)

የጉድ አገር!

“ጉዳዩ ያሳሰባቸው የትግራይ ተወላጆች” የበታችነት ስሜቱን “በወታደራዊ የበላይነት” ለማሳየት ወያኔ ከቀድሞው አሳዳሪው ከሻዕብያ ጋር ባደረገው የእብሪት ጦርነት ሳቢያ “ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግራይ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠየቁ። ለወያኔ ኪሳራ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲከፍል የሚጠየቅባት አገር! ግፈኞች!

Image result for tigray oppression

Photo Credit: Satenaw website (The Ethiopian rulers from TPLF)

የጠያቂዎቹ መቆርቆር ግላዊ ሳይሆን ሰብዓዊ ቢሆን ኖሮ ማቅረብ የነበረባቸው አቤቱታ ግፈኛው የወያኔ አገዛዝ የበታችነቱ ወይም መንፈሰ ደካማነቱ የሚሽርለት መስሎት በገባበት ጦርነትና እስካሁን ስላጠፋው ጥፋት፤ “ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነች” ብሉ አደባባይ ወጥተን እንድንጨፍር ስላደረገው አገዛዝና አካባቢውን ለሁለት አስርት አመታት ያህል የጦርነት ቀጠና በማድረጉ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ከስልጣን እንዲወርድ መጠየቅ ነበረባቸው።

ወያኔዎች የሻዕብያ ጀሌ ሆነው አዲስ አበባ እንደገቡ “ሽግግር” ባሉት ወቅት ባዘጋጁት ቻርተርና “ሕገመንግሥታዊ ሰነድ” “የልማት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች” የሚል አንቀጽ በማስገባት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ኅሊናዊና ቁሳዊ ሀብት ወደ ትግራይ በማፍሰስ ትግራይን “የአፍሪካ ታይዋን” ለማድረግ ቀን ተሌሊት ሲሰሩ እንደከረሙ ለቀባሪው ማርዳት ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለተጎዳው አካባቢም “የልማት ቅድሚያ” እና “ልዩ ድጎማ” ሲሰጠው እንደነበር ያለፉትን የኢትዮጵያ አስራ አምስት በላይ አመታት የበጀት አመዳደብ ቀመር ለምናውቅ ግልጽ ነው። እንግዲህ “ጎበዞቹ” “ጉዳዩ ያሳሰባቸው የትግራይ ተወላጆች” የሚጠይቁት ወያኔ ባለፉት ሀያ አመታት አካባቢ “የልማት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች” እያለ የአገር ሀብት ወደ ትግራይ ሲያሸሽ ከነበረው ተጨማሪ ነው።

“ጎበዞቹ” ትግራይ እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው በጦርነቱ የተጎዳው መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ሀገሪቱ እንጂ አንድ ክፍለ ሀገር ብቻ እንዳልነበረ ስናስታውስ ነው። “ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው በጦርነቱ ሰማንያ ሺህ ልጆቻቸውን የገበሩ ኢትዮጵያውያን ወላጆች እድሜ ልካቸውን በልጆቻቸው ሞት ተጎድተው መኖራቸውን ስናስታውስ ነው።

“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው የትግራዩ ወያኔ በጫረው ጦርነት ወደ ሰማንያ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ረግፋውና ሰማንያ ሺህ እናቶችና አባቶች ያለጧሪ፤ በመቶ ሽዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ደግሞ ያለ ወላጅና አሳዳጊ ቀርተው የሚያስታውሳቸው ጠፍቶ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ስናስታውስ ነው።

“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው ሁለት አመት በፈጀው የወያኔና የሻዕብያ ጦርነት የመላው ኢትዮጵያ በጀት ለጦርነቱ ይውል ሲውል እንዳልነበር ትግራይ ብቻ እንደተጎዳች ተደርጎ ተለይታ ትካስ ተብሎ መቅረቡን ስናስታውስ ነው።

“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው በጦነተ ለተጎዱ አካባቢዎች እየተባለ የበጀት ቀመር ወጥቶለት ከኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት ጦርነት ወደተካሄደበት “ክልል” ፈሰስ ይደረግ እንደነበር ስናስታውስ ነው።

“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ምጸት የሚሆነው ወያኔ የሚመራው “መንግስት” “ወዲ አፍሮ” ለስልጣኑ አደጋ ስለሆነ አስመራ ድረስ ዘምቶ ያስወግደው ዘንድ በትግርኛ ሲማጸኑ የነበሩ ጦርነት ናፋቂዎች መሆናቸውን ስናስታውስ ነው። የጉድ አገር!

*********

Image result for irreecha massacreImage result for irreecha massacre

Photo: Agazi Army in action at Irreecha Massacre

የትግራይ ተወላጆች “በጦርነት ሳቢያ ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን የጠየቁበትንና በአውራምባ ታይምስ ላይ የወጠውን ከዚህ በታች ያንብቡ።

Concerned Individuals and Social Media Activists Write Open Letter to PM Hailemariam on Repercussions of “no peace, no war policy” in Tigray

By admin · January 13, 2017

Awramba Times (Addis Ababa) – A group of social media activists and concerned individuals from Tigray have written an open letter to FDRE’s prime minister, Hailemariam Desalegn, voicing their concerns about “no peace, no war policy” and its repercussion on the overall development and investment opportunities in Tigray. The activists also asked on their letter that the war-torn province of northern Ethiopia should get possible benefits and compensations from the federal government to recover from the calamitous damages it faced in nearly two decades. Please read the amharic open letter below.

——————————————

ለክቡር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር
ኣዲስ ኣበባ

ጉዳዩ፡ በኢትዮ ኤርትራ ዳር ድንበር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የተከተለው ሰላምና ጦርነት የሌለበት ፖሊስ በትግራይ ክልል እያደረሰ ያለው ጉዳት የሚያካክስ እርምጃን ይመለከታል።

የትግራይ ህዝብ ኣምባገነኑን የድርግ መንግስትና ኣግላይ ጠቅላይ ስርኣት ገርስሶ እኩልነትና ፍትሃዊነት የተረጋገጠበት ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርኣት ለመመስረት ባካሄደው እልህ ኣስጨራሽ የ17 ኣመት ትግል ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ከህይወት መስዋእትነት ባሻገር ማህብራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመሰረት ልማት ተቋማቱ ወድመዋል፣ ከዚህ በተጨማሪ ለ17 ኣመት ምንም ግንባታ ሳይደረግባቸው ቆይተዋል፡፡ የተግራይ ህዝብ ለስደት እና ለሰው ሰራሽ ረሃብ በመዳረጉ የህዝቡ ማህብራዊ ግንኙነትና ህይወት ተቃውሷል፡፡

ኣምባገነኑ የደርግ መንግስትና ጠቅላይ ኣግላይ ስርኣት ከተገረሰሰ በኋላ የትግራይ ህዝብ ባገኘው ኣንፃራዊ ሰላም ታግዞ ፊቱን ወደ ልማት በማዞር ክልሉንና ኣገሪቱን ለመገንባት በትጋት ተሰማርቶ ነበር፡፡ በትግራይ ክልልና ህዝብ ላይ የደረሰው የተቋማት፣ የመሰረተ ልማት ውድመት ለማገገም ብዙ ጥረት፣ ጊዜና ሃብት የሚፈልግ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የትግራይ ህዝብ የሰው ሃይሉን ኣቀናጅቶ በውስን ሃብት የክልሉን ገፅታ ለመለወጥ በወኔና በእልህ ተንቀሳቅሷል፡፡ ነገር ግን ያለፈው የእርስ በርስ ጦርነት ካደረሰበት ጉዳት ሳያገግም በህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ (ህግዴፍ) የሚመራው የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ተፅእኖ ለማሳደር በትግራይ በኩል በከፈተው ወረራ የትግራይ ክልል ዳግም የጦርነት ቀጠና ሊሆን ችሏል፡፡ የኤርትራ መንግስት ወረራ በኢትዮጵያ ህዝብ የተባባረ ክንድ ቢቀለበስም የትግራይ ክልል መስተዳድርና ህዝብ ግን የሁለቱ መንግስታት ፀብ እልባት ባለማግኘቱ ወረራው ያስከተለውና እያስከተለ ያለው የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ከፍተኛ ቀውስ በቀጠይነት ተሸክመውት ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የተከተለው ጦርነትና ሰላም የሌለው ስትራቴጂ በትግራይ ክልል በተለይ በኣጎራባች ወረዳዎች ቋሚ የፀጥታ ስጋት ፈጥሮ ክልሉ ኢንቬስትመንት የማይስብና ህዝቡ ያልተረጋጋ ህይወት የሚመራ ኣድርጎታል፡፡ የኤርትራ መንግስት ሰራዊትና በኤርትራ የተጠለሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል ሰርገው በመግባት ወጣቶችን እያፈኑ ይወስዳሉ፣ የህዝቡን ንብረት ይዘርፋሉ፣ ግለሰቦች ይገድላሉ፣ ኣካባቢውም ለህገ ወጥ የሰዎች ንግድና ስደተኝነት ኣመቺ ሁኔታ በመፍጠሩ ወረራው ያስከተለው ማህብራዊ ቀውሱ ቀጣይ እንዲሆን እድል ፈጥሯል፡፡ ኤርትራ መንግስት ኣፍኖ የወሰዳቸው ዜጎች በክልሉ ተጨማሪ ማህበራዊ ቀውስ ፈጥሯል ፡፡ ኣገሪቱን ሉኣላዊነት ለመጠበቅ በክልሉ የሰፈረው የሃገር መከላከያ ሰራዊትና ከኤርትራ የመጡ ስደቶች በክልሉ የተፈጥሮ ምህዳር ላይ የሚፈጥሩት ጫና ቀላል ኣይደለም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የተከተለው ጦርነትና ሰላም የሌለው ስትራቴጂ ላለፉት 15 ኣመታት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም በቅርቡ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስትዎ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ እቅድ እንደሌለው ኣብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከኤርትራ መንግስትና በኤርትራ የተጠለሉ የፖለቲካ ሃይሎች የሚፈጥሩት የፀጥታ ስጋትና ማደፍረስ የመከላከሉ ሚና በትግራይ ሚሊሻ ትከሻ ላይ እንደሚወድቅ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ የክልሉ ሚሊሻ ቤተሰብ የሚመራና በመንግስት ደመወዝ የማይከፈለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሚሊሻው የመከላከል ተግባር ላይ ሲሰማራ ከእርሻውና ከሌላ ተግባሩ መፈናቀሉ ኣይቀርም፡፡ በዚህ ምክንያት የሚሊሻው ቤተሰብ ኑሮ ይናጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የክልሉ ህዝብ ከኤርትራ መንግስትና በኤርትራ የተጠለሉ ተቃዋሚ ሃይሎች ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት ብቻውን እንዲሸከም እየተፈረደበት ነው ማለት ነው፡፡

በዚህ መሰረት በኢህኣዴግ መራሹ ፌዴራል መንግስት ጦርነትና ሰላም የሌለው ፖለሲ ላለፉት ኣስራ ኣምስት (15) ኣመታት በትግራይ ህዝብና ክልል ላይ እየደረሰ ያለው የኢንቬስትመንት እጦት ፣ የመሰረት ልማት መጓተትና፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ኪሳራ የሚያካክስ ድጎማ ያስፈልገዋል፡፡ ኢህኣዴግ መራሹ የፌዴራል መንግስት የትግራይ ክልልና ህዝብ ላይ ኪሳራ እያደረሰ ያለው ጦርነትና ሰላም የሌለበት ፖሊሲ የማይቀይር ከሆነ ጉዳቱን ለማካካስ የሚያስችል የበጀት ድጎማና ኢንቬስትመንትን ሊያበረታታ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታና ዋስትና የማቅረብ ሃላፊነትና የሞራል ግዴታ ኣለበት፡፡ ዋነኛውና ኣስተማማኙ መፍትሄ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግስታት ያለው ጦርነትና ሰላም የሌለው ሁኔታ ለኣንዴና ለመጨራሻ እልባት እንዲገኝ ማደረግ ነው የሚል እምነት ኣለን፡፡ ነግር ግን ጉዳዩ እልባት እንስኪያገኝ ድረስ መግስትዎ የሚከተሉትና ሌሎች በዚህ ደብዳቤ ያልተጠቀስናቸው ተግባራት በትግራይ ክልል እንዲከናውን በኣክብሮት እንጠይቃለን፡፡

1. የ17 ኣመቱ የእርስ በርስ ጦርነት ያደረሰው ሰብኣዊ፣ ማህብራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሳያገግም የኤርትራ መንግስት በኣገራችን ያካሄደው ወረራ እና ቀጣይ የኢህኣዴግ ጦርነትና ሰላም የሌለው ፖለሲ ላለፉት 15 ኣመታት በክልሉ እያደረሰ ያለውን የመሰረት ልማት ግባታ መጓተት፣ ማህራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቋቋም የሚያስችለው ለትግራይ ክልል መስተዳድር ልዩ የበጀት ድጎማ እንዲደረግለት፣

2. በትግራይ ክልል ኢንቬስትመንትን ሊያበረታታ የሚችሉ የመሰረተ ልማት ግንባታና በክልሉ በኢንቬስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለ ሃብቶች የፌዴራል መንግስት ዋስትና እና ልዩ የበድር ኣገልግሎት እምዲያመቻችላቸው ይደረግ፣

3. በተለይ በትግራይ ክልል ያለው የስልክ፣ የውሃና የመብራት ኣቅርቦት ኢንቬስትመንትን እያሸሸ ስለሆነ በኣፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ ይደረግ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ከ10 ኣመት በፊት የመቐለ የውሃ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት ብድር ኣፈላልጎ እንዲገነባ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ስራ ኣስፈፃሚው ወደ ተግባር ሊመነዝረው ስላልቻለ በመቐለ እና በሌሎች የትግራይ ከተሞች ለኢንዱስትሪው ፓርክና ሌሎች ልማቶች ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ ያለው የውሃ ኣቅርቦት እጦት ነው፡፡

4. በፀጥታ ማስጠበቅ ላይ የተሰማሩ የትግራይ ሚሊሻ ኣባላት የፌዴራል መንግስት ደመወዝ እንዲከፍላቸውና የክልሉ የፀጥታ ሃይል በሰው ሃይልና በመሳሪያ የተሟላ ትጥቅ እንዲኖረው እንዲደረግ፡፡ የኤርትራ መንግስት ኣገራችንን ሲወር የትግራይ ክልል ሚሊሻ ባልተሟላ ትጥቅና የሰው ሃይል ለመከላከል ባደረገው ጥረት የተከፈለው ከፍተኛ ዋጋ እንደገና መደገም ኣይኖርበትም፣

5. የፀጥታ ስጋትና የኤርትራ መንግስት ወታደሮችና በኤርትራ የተጠለሉ የፖለቲካ ሃይሎች እንቅስቃሴ የኤርትራ ኣጎራባች ነዋሪ ዜጎቻችን ላይ የሚፈጥሩት ያልተረጋጋ ኑሮ የሚቋቋሙበት የጤና፣ ትምህርት ቤት፣ የውሃ ኣቅርቦት ወዘተ ግንባታ እንዲከናወን፤

ከሰላምታ ጋር
ጉዳዩ ያሳሰባቸው የትግራይ ተወላጆች

ግልባጭ፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት
ኣዲስ ኣበባ
ለትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር
ለትግራይ ክልል ምክር ቤት
መቐለ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s