ቢሊሱማ በነፃ አይገኝም (ተስፋዬ ገብረአብ / Gadaa Gebreab)

ቢሊሱማ በነፃ አይገኝም

ከተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)

የሰው ልጅ ይወለዳል፤ እንደ ዛፍ አርጅቶ ይሞታል። ስርአትም እንዲሁ፤ የተፈጥሮ ህግ ነው። ከመቶ አመታት በሁዋላ በህይወት የለንም። ሌሎች ግን ይኖራሉ። ታሪክ ብቻ ይቀራል። ጥይት ቢስተን ባይሎጂ አይስተንም። መስዋእትነት ሲከፈል ተተኪው ነፃነት መውረሱ አይቀርም። በቢሾፍቱ ከተማ፣ በሆራ አርሰዲ ደረት ላይ፤ በአድአ ጥቁር ሁዳድ – የተሰዋችሁ የኦሮሞ ልጆች – እንኳን ደስ ያላችሁ!! ታሪክ ሰርታችሁ – ታሪክ ሆናችሁዋል!!

ዝንተ አለም ሲሞት ነበር ኦሮሞ! በማይመለከተው ጉዳይ! የራሱ ባልሆነ አደባባይ – ሲሰዋ ኖሯል ኦሮሞ። ቢሾፍቱ ላይ መውደቅ ምርቃት ነው። ከሆራ ደረት ላይ መንሳፈፍ ፀጋ ነው። በራስ አጀንዳ መሰዋት፤ በራስ መሬት ላይ መደፋት – ክብር እንጂ ሃዘን አይደለም። ቢሾፍቱ ለቄሮ አገሩ ነው – አጀንዳው የራሱ ነው – ጋራና መልካው የግሉ ነው – ቢሰዋ ባገሩ ላገሩ ነው። አድአ በርጋ ስጋው ነው። ባቦጋያ ደሙ ነው። ፎቃ አያቱ ነው። የቱለማ እምብርት ነው። የበከጆ አባገዳ – የቁርቁራ ኩታገጠም – የኩሪፍቱ ገደም ገደም፤ ሲተኮስበት ባልባሌ፤ በእሬቻ እለት ዋዜማ – ማቅ ሲለብስ ኦሮሙማ – ከበሰቃ እስከ አዳማ – ከቱሉፈራ እስከ ጉምጉማ – ቄሮ ደረቱን ገልብጦ – ከበደገባቤ እስከ ሉጎ፤ ከበልበላ ሸምጥጦ – ሲሰዋ በሁዳዱ፤ ዋቃ ሁሉን ያይ ነበር – ጊዜ ይመጣል – አይዛነፍም ፍርዱ።

ጭቋላ ከዋቃ በታች – ሁሉን ያይ ነበር። ቄሮ ልቡ ሲበሳ በአረር – ከፉርጉጌ ጭምር። ከኢሉ አባቦራ የመጣ ቄሮ – ከመጫ የመጣ ቄሮ – ከቱለማዎች ሊውል አብሮ – ወጉን ሊያወጋ አድሮ – ከደንገጎ የወረደ ጎረምሳ – ከሮቤ ወገኑ ሊያወሳ – ሊጫወት ዳንጋላሳ – ነበር አመጣጡ። ሌላ ጥያቄ አልነበረውም። ከቢሊሱማ ሌላ? – ከቶ ምን ጥያቄ ይኖረዋል? ትንሹ ጥያቄ እሱ ነው። ሲወለድ ጀምሮ – ያገኘው ከተፈጥሮ – ጥያቄው አንድ ነው – ከአምና እስከ ዘንድሮ!!

የአግአዚ ጥይት ሲዘራ – እነ ቦንቱ ሲሳቀቁ – እነ ቄሮ ወርቁ – እነ ጋሜ ትጥቁ – ሞትን ንቀው ሲስቁ – እያወቁ ሲወድቁ – ምን ተሰማህ ጉዳ ሃይቅ ጥልቁ? ምን ተሰማህ ኪሎሌ – የእነ ጅሩ ጉርሜሳ ቀበሌ – ምን ተሰማህ አርሰዲ? ምን ተሰማህ የረር! የኦሮሙማ ሻኛ – የዋጂቱ አደ ማኛ – ነባር የቱለማ ዳኛ! ቄሮ ሲጋደም አጣምሮ መስቀለኛ!! ምን ተሰማህ ቢርማጂ? ቄሮ ሲወድቅ በደረቱ – ከእነ እህቱ – አደ ኦሮሞ ልጇ ሲወድቅ ተመትቶ፣ “ሌላም ልጅ አለኝ – የሚወድቅ” ብላ ስትናገር በቁጣ፣ ምንተሰማህ የፎቃው አባ ፊጣ? ምን ተሰማህ ቢሾፍቱ? እንግዶችህ ደጃፍህ ላይ ሲሞቱ? መቸም ሁሉን አይተሃል – ባይንህ በብሌኑ – ባይንህ በብረቱ። ቢሾፍቱ ልበ ጥልቁ – እስኪ የልብህን ንገረኝ? ሚሊዮናት ወገኖችህ አድአን ሲያጥለቀልቁ – በእሬቻ ዋዜማ ማታ – በአንድ ልብ ህብረ ቱማታ – በሰላም እየዘመሩ – ሲሳብባቸው ቃታ – በልበቢስ እሩምታ – ምን ተሰማህ ቢሾፍቱ!? ቢሊሱማን ለኩሳችሁ – በፀጥታ ያረፋችሁ – የምትኩ ልጅ አቦማ – የቱምሳ ልጅ ባሮ – የመዘምር ልጅ ማሞ – መንፈሳችሁ ተሳቀቀ? ወይስ ጊዜው እንደደረሰ ቆሌያችሁ አወቀ?
እኔ ሩቅ ነበርኩ። ብቻ በሩቅ ሁሉን አያለሁ። ቢሾፍቱ በደም ስትታጠብ – የአግአዚ ጠመንጃ እሳት ሲታለብ – ጄኔራል ገብረዲላ ጨንቆት ሲካለብ – ሩቅ ሆኜ ታዘብኩ። ብቻዬን አልነበርኩም። እሬቻ አክብረን ስንመለስ – ከመልካ ጋር፣ ከኦሉማ ጋር፣ ከቀጄላ ጋር የእሬቻ ጠበል ልንቃመስ – አብረን ነበርን። ዜናው ሲሰማ – ኦሉማ አባ ቢሎ – ትንፋሽ አጣ ልቡ ቆስሎ። እኔም አየሁ – አቀርቅሬ – በማውቃቸው በእነዚያ ሰዎች – በእነ እፍረተቢስ አፍሬ – ሁሉን አየሁ በስጋት – የነገውን በቀል በመፍራት! የነገውን አደጋ በማሰብ – በጭንቀት!!

የእንትና ልጅ እንትና – የእከሌ ልጅ እከሌ – የእንቶኔ ልጅ እንቶኔ – እባካችሁ ፈገግ በሉ – የኦሮሞ ልጆች ቀና በሉ። ማዘን አይገባም። በግልባጩ መቅናት ይገባል። ለቢሊሱማ ደረቱን የሰጠ ያስቀናል። በነፃ የሚገኝ ቢሊሱማ የለም። በጢኖ ሆራ ደረት ላይ የተንሳፈፈ ቄሮ – እድለኛ ነው። የዛሬ ጀግና ነው። የነገ ታሪክ ነው። የነገ ቢሊሱማ ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s