አዲስ ገጽ መጽሄት: ‹‹ኦሮሞ ጀግና ነው!››

‹‹ኦሮሞ ጀግና ነው!››

አናንያ ሶሪ (አዲስ ገጽ መጽሄት)

‹‹ኦሮሞ ጀግና ነው!›› ማለት፡- እንደ ሕዝብ መገለጫው የሆነውን ገዢ ባህርይ መናገርና ማወጅ ነው፡፡ ለዘመናት በብዙ ፈተናና ዕድሎች ውስጥ ያለፈው ይህ ትልቅ ሕዝብ የገድሉን ያህልም ያልተነገረለት ነው፡፡

ዛሬ በዚህ ጽሁፍ፡- በግሌ ለዓመታት ከነበሩኝ ዕይታዎችና አስተውሎቶች ተነስቼ ይህን ድንቅ ሕዝብ ለማመስገን ለመዘከር እና ለማወደስ ወደድኩ…

ቢቻለኝም፡- በተከታታይ በአገራችን ስለሚገኙ ማሕበረሰቦች መጻፌን እቀጥላለሁ፡፡

ነገር ግን፡- ይህ እዚህ የሰፈረው ሃሳብ የግል ምልከታዬ እና ግንዛቤዬ ላይ የተመረኮዘ፣ ከአብሮ መኖር ባህር የተቀዳ፣ ካጋጠሙኝና ካየኋቸው ማህበራዊ ተሞክሮዎች የፈለቀ አስተያየቴ ነው፡፡ ሰፊውን የኦሮሞ ታሪክ ግን ለባለሙያዎች እተዋለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ምስረታም ሆነ ግንባታ ሂደት ውስጥ በየዘመናቱ የራሱን አሻራ ያሳረፈው ይህ ‹‹ታላቅ ሕዝብ››፤ ከወንድም የሌላ ብሔር ህዝቦች ጋር የሰራውና የተጋራው እጅግ ብዙ ወርቃማ ታሪክ ባለቤት ነው፡፡ ከሀገሪቱ መልክአ-ምድር ውስጥም ሰፊውን ስፍራ በመያዝ ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ጋር በጋብቻ፣ በባህል፣ በእምነት፣ በግብይት፣ በጦርነት፣ በንግስና ተደባልቆ ተዋህዷል፡፡ በተለይ ለአብሮ-መኖር ሲል ረጅም ርቀት የሚጓዘው ‹‹ኦሮሞ›› ሁሌም እጅግ ያስደንቀኛል፡፡ እጅግ ሰው-ወዳድነቱ ……. ፈጣሪን አክባሪነቱ……. ተፈጥሮን ተንከባካቢነቱ ….. ብቻ ምኑ ተነግሮ ምኑ ይተዋል?!

ኦሮሞ – ዛፍ ይወዳል፤ ኦሮሞ ባህር ይወዳል ! ምድሩን ይወዳል፤ ሰማዩን ያፈቅራል! ኦሮሞ ፈጣሪንና ፈጣሪ የፈጠረውን ፍጡር ሁሉ ከልቡ ያፈቅራል! ኦሮሞ – ላሞቹን በሬዎቹን፣ እጽዋቱን አእዋፉን፣ ሳሩን ቅጠሉን ከህልውናው ጋር አዛምዶ ይኖራል፡፡

ኦሮሞ – የሕይወትን ጣዕም በሚገባ ይረዳል፡፡ ጥፍጥናን እና ምሬትንም እንዳመጣጣቸው በፀጋ ይቀበላል! ውልደቱ፣ ሰርጉና ሕልፈቱ በጀግኖች ጌረርሳ ይታጀባል! በሳቁና ለቅሶው፣ በደስታና ሀዘኑ ከልቡ የተሰማውን ከነፍሱ የፈለቀውን… መንፈስን በሚነካ ጥዑም ዜማ ያንጐራጉራል፡፡

በሰፊ ጀግንነቱ እና በሰፊ ፍቅሩ ሰፊ ግዛት የያዘው ‹‹ኦሮሞ›› የትንሽነት ስነ-ልቦና ጭራሽ አያውቀውም፡፡ በትልቁ ደክሞ… ወዙን አንጠፍጥፎ… ትልቅ ሀብት ያፈራል፡፡ ካፈራው ሀብት ሁሉ ይልቅ ግን ‹‹ዋቃ / እግዚአብሔር›› ትልቅ እንደሆነ ያውቃል፡፡ አምላኩንም እርጥብና የለመለመ ሳር ይዞ በረጋ ባህር ዙሪያ ቅዱሱ መንፈስ በረበበበት ላይ ተስብስቦ፤ ምስጋናውን ጸሎቱን፣ ምልጃውን ተስፋውን፣ ህልሙን፣ የትላንቱን፣ የወደፊቱን፣ የልቡን፣ የነፍሱን፣ መሻት ያሳርጋል፡፡ የማቲዎቹን ነገር…. የከብቶቹን ነገር… የሰብሉን ጉዳይ…. የአገሩን ነገር….. የሕዝቦቹን ሰላም…. ሁሉ አደራ ይላል! ‹‹አቤቱ….ዋቀዮ፡- አንተ በእነዚህ ሁሉ ውስጥ አብረኸን ሁን! ከጎናችን ቁም!›› ብሎ እግዚዖ ይላል… ኦሮሞ አምላኩን ጠንቅቆ ያውቃልና! ኃያልነቱም ከአምላኩ ጋር ባለው ጽኑ ፍቅር የተነሳ ነውና!

ኦሮሞ – ፍቅሩም ጀግንነቱም ‹‹ደማቅ›› ነው! ደማቅ ቀለምም ሁሉ የፅኑና ኃያል ጥልቅ-ስሜቱ /Passion መገለጫ ነው፡፡ ኦሮሞ – ለፍቅር እንጂ ለስስት ቦታ የለውም፡፡ ንፉግም አልነበር፤ ንፉግም አይደለም! የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብቱን ከማንም ጋር ተካፍሎ መብላትን ያውቅበታል፡፡ ኦሮሞ ልቡም ትልቅ ፍቅሩም ትልቅና ጥልቅ ነው፡፡ ‹‹ፍጹም ፍቅር›› እንጂ ግማሽ መውደድ የሌለው የሰው-ንፁህ ነው፡፡ በልቡ ሌላ እያሰበ ባንደበቱ አይሸነግልም – ሲወድም ሲጠላም ፊት ለፊት ነው፡፡ ድብቅነትና መሰሪነት ተፈጥሮው ውስጥ የሉም! ኃይሉም፡- ለአምላክ፣ ለተፈጥሮና፣ ለሰው-ልጆች ሁሉ ካለው ጥልቅ ፍቅር ይመነጫል! አምላኩን ያምናል፤ ተፈጥሮን ይጠብቃል፤ የሰው-ልጆችን ይወዳል! ያቅፋል እንጂ አይገፋም፤ ያካትታል እንጂ አያገልም ! የራሱ ያደርጋል……. ያላምዳል እንጂ ማንንም ባእድ/ Alien አያደርግም! ኦሮሞ ለጋስና ቸር ነው! ቸርነቱም ከቸር-አምላኩ የመነጨ ነው፡፡

ኦሮሞ – እጅግ ኃላቀር በነበረው የፊውዳል የድንቁርና ዘመን እንኳን፤ አወቅን ጻፍን ያሉት እኩይ ገዢዎችና ቀላጤዎቻቸው በአፍ ‹‹ፍቅርን›› ሲሰብኩት እሱ ግን በተግባር ‹‹ፍቅርን›› ገልጦታል፡፡ ፍቅርን ቀድሞዉኑ በኑሮው ያውቀዋልና! ኦሮሞ ‹‹ሁሉን ሰብሳቢ›› ነው፤ የሌላ የሚለው የሰው ዘር የለም፡፡ ሁሉንም እንደራሱ ያያል፡፡ ኦሮሞ የትኛውንም ሰው ይቀበላል፡፡ ኦሮሞ ያላሳደገው፤ በፍቅሩ የገዛ ገንዘቡ ያላደረገው በአራቱም አቅጣጫ ቢኬድ አይገኝም ፡፡

ኦሮሞ – ሰፊ ነው፤ ልቡም ዕይታውም ሰፊ ነው! ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያልሸፈነው ጂኦግራፊያዊ ክልል /መልክዓ-ምድር አይገኝም፡፡ ያልተጋባው፣ ያልተዋለደው፣ ያልተዋሐደው የዘር-ግንድም የለም፡፡ በሰፊ ፍቅሩ ያልነካውና ያልማረከው የሰው ልጅ ወገን አይገኝም፡፡ ሁሉን እንደራሱ ለመቀበል የማይቸግረው የፍቅር ሀብታም የመንፈስ በረከቶች ሁሉ ባለ-ጸጋ ነው፡፡ ኦሮሞ ትልቅ ነው! ከየትኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ-አለም የሚበልጥ ሀገር-በቀል ማህበራዊ ስርዓት ባለቤት ነው ፡፡ ‹‹ገዳ፣ ሞጋሳ፣ ጉዲፈቻ፣ ጉማ….›› ለዚህ ህያው ምስክር ናቸው ፡፡

ኦሮሞ ጀግና ነው! ጀግናንም ይወዳል፡፡ የኦሮሞ ጀግና ለፍቅር እንጂ ለሌላ ለምንም አይገዛምም፡፡ በተንኮል ለተነሱበትም በኃያል ክንዱ የስራቸውን ለመስጠት አንዳች አይቸግረው፡፡ ኦሮሞ ፈረሰኛም ነው! ጉግስ ጨዋታም ሁለተኛ ተፈጥሮው! ኦሮሞ – የንስር መንፈስ ያለው ኃያል ስለሆነ ‹‹ከፍታን›› ቤቱ አድርጓል! ዘሩም በምድር ላይ በዝቷል፤ የረገጠው ሁሉም ይለመልምለታል፡፡ ድልንም በአምላኩ ፈቃድ ተቀዳጅቷል፡፡ ከሰው ልጆች ሁሉም ተወዳጅቷል! ኦሮሞ አዋቂ ነው፤ አስተዋይ ነው! ፍትሀዊና ፍርድ-አዋቂ ጭምር ነው፡፡

ኦሮሞ – ሁሉም የሚጠለልበት ‹‹ትልቅ ዋርካ›› ነው! ኦሮሞ ‹‹ግንድ›› ነው፤ ቅርንጫፎቹ በሙሉ የሚያያዙበት! ኦሮሞ፡- የኢትዮጵያ አንድነት ‹‹ጽኑና ሕያው መሰረት›› ነው፡፡
ኦሮሞ – ታላቅ ማዕበል ነው! በፍቅሩና በጀግንነቱ ምድሩን ሁሉ ያጥለቀለቀ !

ኦሮሞ፡- ስለነጻነት፣ ስለእኩልነት፣ ስለማህበራዊ ፍትህ ደሙ እንደጅረት የሚፈሰው ነው!

ኦሮሞ፡- በምድሩ የሰው ልጆች ሁሉ በሰላሙ እና በጥበቃው ጥላ ስር የሚያድሩበት ታዛ ነው! ኦሮሞ ‹‹ቤቱ›› የሁሉም ነው!

ኦሮሞ፡- ‹‹አሸናፊ›› ነው! ስነ-ልቦናውም ቀዳሚ እና የከፍታው ማማ ላይ ርቆ የተሰቀለ ነው፡፡ ቁመናውም ላይ ያለን እንጂ ታች ያለን በትይዩ እንዲያይ አይፈቅድለትም! ኦሮሞ – አበበ ቢቂላ ነው! ኦሮሞ፡- ታደሰ ብሩ፣ ማሞ መዘምር ነው! ኦሮሞ፡- አብዲሳ አጋ፣ ጸጋዬ ገ/መድህን ቀዌሳ ነው! ኦሮሞ – ደራርቱ ቱሉ፣ ዋሚ ቢራቱ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ በቀለ ወያ፣ አብቹ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ አሊ ቢራ፣ ኤቢሳ አዱኛ፣ ይልማ ደሬሳ፣ ራስ መኮንን ጉዲሳ …… ሁሉ ናቸው!

ኦሮሞ – በጀግንነቱ ሁሌም ‹‹ከፍታው›› ላይ እንደሚገኝ የዳልጋ-አንበሳ ነው! ኦሮሞ፡- አባ ዶዮ፣ ጎበና ዳጩ፣ አባ ጅፋር፣ ጆቴ ነው! ኦሮሞ፡- ምንትዋብ፣ ጣይቱ ብጡል ወሌ፣ ‹‹ሚኒሊክ›› እና ‹‹እያሱ›› ብሎም ‹‹ኃይለ-ስላሴ››ም ጭምር ነው! ኦሮሞ – መለኛው ኃይለ-ጊዮርጊስ ዲነግዴ ነው! ኦሮሞ – መንግስቱና ገርማሜ ነዋይ፣ ተፈሪ በንቲ፣ ደምሴ ቡልቶ፣ ካሳዬ ጨመዳም ነው! የእውቀት ፋኖሱ ሰማዕት ‹‹ኃይሌ ፊዳ›› ነው! ተመራማሪና አሰላሳዩ ‹‹ሌንጮ ለታ››ም ነው! የአብሮ መኖር መሐንዲሶቹ ‹‹መረራ ጉዲና›› እና ‹‹በቀለ ገርባም›› ናቸው!

ኦሮሞ – አዛኝና ሩህሩህም ነው! ኦሮሞ የአበበች ጎበና አባት ነው፤ በክፋት የበለጡትን በፍቅር በልጦ የሚኖር የመለኮታዊ ጥበብ ባለቤትም ነው – ኦሮሞ! ስለእውነተኛ ፍቅር እንጂ ስለፍቅር ስብከትና ዲስኩር ስለማይጨነቅም፤ ይኸው ‹‹ጥልቅ አፍቃሪነቱ››፣ ‹‹ሰው ወዳድነቱ››፣ ‹‹ታሪክ ሰሪነቱ››፣ በቃየላውያን ሁሉ ሊደበቅና ሊደፈቅ ተሞክሯል፡፡

የዘመኑ ቃየላውያንና ይሁዳውያንም ስብእናውን ሊገድሉ፣ ቸርነቱንና ደማቅ ታሪኩን ክደው ሊያጠፉ ብሎም ህልውናውን ሊሰርዙ በክፋት ተነሳስተውበታል፡፡ ከመሬቱ ሊነቅሉት፣ ከቀዬው ሊፈነቅሉት፣ አምላኩን ከሚያወድስበት ሊነጥሉት፣ ምድሪቱን አርሶና በወዝ በድካሙ ጥሮ ግሮ የሚያፈራውን ፍሬ እንዳይበላ አመድ አፋሽ ሊያደርጉት የክፋት ጦራቸውን ሰብቀው እየነካኩት ነው፡፡ ስለ‹‹ትልቅነት››፣ ስለ‹‹ትልቅ ሕዝብነት››፣ እና ስለ ‹‹ትልቅ አምላክ›› የማያውቁ ዝቅተኞችና አናሳዎች የትልቅነት ካባውን ለመጎተት አድብተው በዙሪያው ተኮልኩለዋል፡፡

ነገር ግን፡- ‹‹ኦሮሞ›› በገዛ አገሩና ምድሩ ላይ የበይ-ተመልካች ሊያደርጉት ሌት-ተቀን የሚያሴሩበት መጤ-ወራሪዎችን እየመከተ ነው፡፡ ከአብራኩ በወጡና እንደገዛ አካሉ ባሳደጋቸው ከሃዲዎች አማካይነትም የተዘረጋውን ‹‹የእጁ አዙር የቅኝ አገዛዝ መዋቅር›› አውድሞታል፡፡ ለም መሬቱን፣ ላቡን፣ የላቡን ፍሬ፣ ወርቁን፣ ቡናውን፣ ውድ ልጆቹን በዘመናዊ-ባርነት ሊጨመድዱ ያሰቡ እኩያንን በገቡበት ገብቶ እየቀጣ ነው! ኦሮሞ ትዕግስቱ አልቋል፤ ኦሮሞ የቻይነት ጥጉ እጅጉን ተፈትኗል፤ ስለዚህም ኦሮሞ ተቆጥቷል!

እንደበጋ መብረቅ እየተወረወረ የጅቦችን ማንቁርት መያዝ የቀን ተቀን ስራው አድርጎታል! ትናንትናም እንዳሸነፈ ዛሬም ድል በመዳፉ ውስጥ ናት!

ይሄ የተጻፈው ሁሉ ተነግሮለትም ‹‹ኦሮሞ›› ገና ምንም ያልተባለለት ነው!

ኦሮሞ ‹‹ጀግና›› ነው! ለዛውም የፍቅር!

ክብር ለ‹‹ኦሮሞ››ይሁን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s