አዲስ-ገጽ: ኦሮሚያ በልጆቿ አሟሟት ደም አለቀሰች! (ኦሮሚያ ዱኣ ኢጆሌሼን ኢገ ቦሴ!)

ኦሮሚያ በልጆቿ አሟሟት ደም አለቀሰች! (ኦሮሚያ ዱኣ ኢጆሌሼን ኢገ ቦሴ!)

ሀብታሙ ምናለ (አዲስ-ገጽ)

የህዝቡንና ወገኑን ግፍ እና መከራ ብሎም የሚደርሰውን ሰቆቃ እንዳላየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ በመሆን ኢትዮጵያዊነቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ ቀንም ሆነ ማታ አሳቡና አዳሩ፡- ጀርመን ውስጥ ስለሚደረገው አፈና ፤ ፈረንሳይ ውስጥ ስለተደረገው ግድያ፤ አሜሪካ ውስጥ ስለደረሰው ፍንዳታ የሆነበት፣ ከማዘን አልፎም ዳስ ጥሎ ለቅሶ መቀመጥ የሚቃጣው አለ፡፡ ምክንያቱም ለእሱ ሰው ማለት በውጭ ያለ ባዕድ ነው፡፡ እዚህችው ሀገሩ ላይ መብቱ ተገፎ፤ በጥይት፣ በሰደፍ አፈር ድሜ የሚበላው፤ በፍትህ እጦት የሚሰቃየው፤ የሚታሰረው፤ ሀገሩ ላይ ጭቆናን ለማስወገድ የሚታገለው ለእሱ ነጻነት የሚሞተው ‹‹ሰው›› አይደለም፡፡

ለእዚህም ማሳያ በኦሮሚያ ምድር ማስተር ፕላኑን በመቃወም አደባባይ ላይ የወጣውን ህዝብ ዝም ጭጭ ለማስባል የሥርዓቱ ቀንደኛ ጠባቂዎች የሰው ደም ማፍሰስ እንደ ተራ ተግባር፣ ሰውን መግደል የዶሮን አንገት ቀንጥሶ እንደመጣል ቀላል ሲያደርጉት ተመልከተናል፡፡ የንፁሃንን ደም ማፍሰስ ከቀን ወደ ቀን መስማት ጆሯችን ተለማምዶታል፡፡ ህዝቡም ከእነዚህ መራር እውነቶች ጋር ያለምንም መቆርቆር ተደላድሎ ተኝቷል፡፡ ይሄ እየተፈፀመ ያለው ፓሪስና ዋሽንግተን ቢሆን ኖሮ የህዝቡ ጩኸት ከፍ ብሎ ይሰማ ነበር፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ በቸልታ ታለፈ፡፡ ሻዕቢያ አይደር ት/ቤትን ያለ ይሉኝታ ሲደበድብ ምንም የማያውቁ የህጻናት በድን (አካል) በቴሌቪዥን መስኮት ሲታይ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለምን ተነሳ?! ሲሉ ወለጋ እና አምቦ የሚኖሩ እናቶች የተፈፀመው ያ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ትግራይ ላይ ቢሆንም በተፈፀመው ግፍ ስቅስቅ ብለው አልቅሰው ልጆቻቸውን ለጦርነት መርቀው ሰደው በኦሮሚያ ልጆች ደም ጭምር ሻዕቢያ ተደምስሷል፡፡

ትላንት የጠላትን ክንድ የሰበሩ እጆች ላይ ዛሬ በትረ ሥልጣኑን በሰፊው በያዙት አካሎች እና ‹‹የኦሮሚያ ወኪል ነኝ›› ብሎ እራሱን ከሚጠራው ኦህዴድ ጋር በመተባበር ጠላት ይመስል ህዝቡ ላይ ተኮሱ፡፡ ይበልጥ ሰቅጣጩ ጉዳይ፡- ‹‹ረብሻ ባስነሱት ላይ ‹‹ህጋዊ›› እርምጃ እንወስዳለን!›› በማለት የህዝቡን ስቃይ እያባባሱ ህዝቡን አሸማቀው መኖር ይፈልጋሉ፡፡ ኢህአዴግ ወደ ህዝቡ ላይ በተኮሰ ቁጥር ነገሮች ተረጋግተው የሚበርዱለት መስሎት ነበር፤ ግን ያ አልሆነም፡፡ እንደውም ህዝቡ አይኑን በደንብ ከፍቶ እንዲያይ በማድረግ ለተጨማሪ የመብት ጥያቄ እንዲነሳ ዳረገው እንጂ! ‹‹መብትን በማንኛውም ሰዓት መጠየቅ መብት መሆኑን›› ያምን የነበረው በህወሓት ዘንድ የሚወደደው ሌ/ኮ ኃየሎም አርአያ ፡- ‹‹ ወደ ህዝቡ የተኮሰ መሪ አበቃለት ማለት ነው›› ብሎ የተናገረውን ዘንግተዋል፡፡ ኃየሎም ይሄን ጉድ ለማየት ባይታደልም የእሱ የትግል ጓዶቹ ግን ወደ ህዝብ ተኩሰዋል፡፡ መተኮስ ብቻ አይደለም ወርቅ የሆነውን ህዝብ ገድለዋል፡፡ የትግል አጋራቸው ምክርን ወዴት ወረወሩት?

በአንዳንድ ‹‹ግራ ገብ›› ፖለቲከኞች በኩል ጨቋኝና ተጨቋኝ ተብለው ሲለፈፍባቸው የነበሩት የኦሮሚያ እና የአማራ ህዝብ ላይ ግድያውን እና አፈናውን አጧጥፎ ሄዶበት የአማራውን አመጽ በማዳፈን ለጊዜው ያረገበው ለማስመሰል ቢጥርም፤ በኦሮሚያ ግን ባልተቋረጠ ሁኔታ የፈጠጠ ጭፍጨፋውን ገፍቶ ቀጥሎበታል፡፡ በአንድ አካባቢ ጥያቄ ያነገቡ ወጣቶች ሰልፍ ሲወጡ ምላሹን ጥይት በማድረጉ ይሄ ያንገበገባቸው የኦሮሞ ልጆች፤ በቀጣዩ ቀን ጉዳዩ እንደ ሰደድ እሳት ሁሉም ጋር ተዛምቶ ጉዳዩ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ሄዷል፡፡ በየቀኑም ለመስማት የሚከብዱ ለማየት የዓይን ብሌናችን የማይፈቅደው ለመናገር የጉሮሮን ትናጋ የሚይዙ ግድያዎች እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ ይሄን ህዝባዊ አመጽ ለማስቆም መንግሥት የወሰደው እርምጃ በጣም የመረረ፣ የከበደም ነው! መጀመሪያ ጥያቄውን እንደ ጥያቄ አይቶ ምላሽ መስጠት ሲገባ በየሚዲያው፡- ‹‹አመፁን ያስነሱት ትንሽ ጽንፈኞች፣ አንዳንድ አካባቢዎች፣ ቀጥሎ ኦነግ›› እያለ ……… ለፈፈ፡፡ ‹‹በአፋጣኝ መፍትሔ እሰጣለሁ›› አለ፡፡

‹‹መፍትሔ የማይሆን መፍትሔ›› ጊዜው ያለፈበት ፋይዳ ቢስ ማረጋጊያ ማቅረብ ለማንም እንደማይበጅ በተለያዩ ጊዜያቶች ታይቷል፡፡ በየቀኑ ሰው መግደል ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አያበርደውም! የሚገሉት ጦር ሜዳ ያገኙትን ከእግር እስከ አፉ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የደርግ ወታደር አይደለም፡፡ ክቡርና ንፁህ የሆነ፤ ፍቅር እና ሰላም ወዳዱን፤ ማንነቱን እንዲሁም ባህሉን የሚያከብር፤ ነገ ከነገ ወዲያ ሀገሩን የሚያስጠራ የኦሮሞ ልጅ ነው፡፡ መንግሥትም ገሎ መፎከር ደርግን ካሸነፋ በኃላ ሊያቆም ይገባው ነበር:: ህዝቡ መብቴ ተነካ ብሎ የሚያቀርበውን ጥያቄ በሚወደው፣ በሚፈቅደው የአነጋገር ዘይቤ በሥርዓቱ ሊፈታለት ግድ ይላል፡፡ መንግሥት ጉዳዩን ችላ ብሎ በእራሱ መንገድ ብቻ መፍትሔ ሊያመጣ ቢውተረተር ነገሮች ሁሉ በአላስፈላጊ መንገድ መሄዳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በክልሉ ላይ ህገ-ወጥ ተግባሮች ሲካሄዱ ህዝቡ ከአሁኑ በባሰ ሁኔታ በነቂስ መውጣቱና መብቱን ለማስከበር መነሳቱ አይቀርም፡፡

መንግሥትም ኃላቀር እርምጃውን መተግበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ያን ጊዜም፡- መሬቷ አኬልዳማ (የደም ምድር) ከመሆን ማን ነው የሚታደጋት!? ዘር ዘርቶ ማጨድ የለመደ መሬት እንዴት ብሎ የልጆቹን ደም ይቀበላል፤ በድን ገላቸውን ምድሪቱ እቅፍ አርጋ የምትቀበለው አፍ ባይኖራትም ምድሪቷ እስከመቼ የደም እንባ ታለቅሳለች? እኛስ የመልካሚቱን ሀገር እና ህዝብ ቁጽረ ገጽን እያየን እንኖራለን?፡፡ ሁሌ እንባዋን ብቻ ለማየት ለምን እንገደዳለን? መፍትሔው በእጃችን ሆኖ ስለምን ደም እንቃባለን? አሁንም መንግሥት ቀድሞት የተጓዘው ህዝብ ላይ ለመድረስ ድሪቶውን አራግፎ በፍጥነት መድረስ አለበት፡፡ የኦሮሚያ ህዝብ ከእዚህ መንግሥት ጋር ተቻችሎ መቀጠል እንደማይችል ልጆቻቸውን በራፋቸው ላይ ለጋ ወጣቶችን በመሳሪያ በመድፋት ማረጋገጫ እራሱ መንግሥት ሰጥቷል፡፡ እንደሌሎቹ ሃገራት መገዳደሉ በዝቶ ሞት ርካሽ እንዳይሆን፤ ችግሩ እየሰፋ ሄዶ መያዣ መጨበጫ እንዳናጣ፤ ይሄ ‹‹የበቃኝ አመጽ›› ወደከፋ ችግር እንዳይገባ የሁላችንም ጥረት የሚያስፈልገበት ደረጃ ደርሷል፡፡

ሰው መሞቱ፣ መገደሉም ይብቃ! ጥያቄዎች በአግባቡ ይመለሱ! የሞቱት ለምን፣ በማን እንደተገደሉ ይጋለጥ! መፍትሔው ያለው በመንግሥት እጅ ላይ በመሆኑ ሁላችንም መንግሥት ወደ ሰላም መንገድ እንዲገባ ማስገደድ አለብን፡፡ ሰላምና ደስታ ለኦሮሚያ ምድር ይሁን!
(ነጋ ፊ ገመቹ ቢየ ኦሮሚያፍ!)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s